Monday, January 28, 2013

“ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ፡፡” አትም ኢሜይል
ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ሰሎሞን መኩሪያ
ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁ.6
በረከቱ ይደርብንና ይህንን ቃል የተናገረ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጅ የሆነው ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በብሉይ ዘመን በቅዱስ ዳዊት ሕይወት የተከወነውን በምስጢር ስቦ አምጥቶ የሰማዕታትን ክብር አጎልቶ ተናግሮበታል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትን እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል አነገሠው፡፡ በዙሪያው የነበሩ ኤሌፍላዊያንን አጥፍቶ ደብረ ጽዮንን /መናገሻ ከተማውን/ አቅንቶ ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን ዳዊት ታመመ፡፡የዳዊትን መታመም ሰምተው፣ ካሉበት ተነስተው የዳዊትን ከተማ በተለይም ቤተልሔምን ከበቧት፡፡ ዳዊት ይህ ሰምቶ “ወይ እኔ ዳዊት! ድሮ ታመምሁና ጠላቶቼ ሰለጠኑ ሲል የኀያላኑን ልቦና ለመፈተን ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች ሦስቱ ማለትም አዲኖን፣ ኢያቡስቴ ኤልያና ርስታቸውን /የውኃ መያዣ/ ይዘው፣ ጦራቸውን አሰልፈው፣ ጠላቶቹን ድል ነስተው፣ ዳዊት ሊጠጣ የወደደውን ውኃ አመጡለት፡፡ቅዱስ ዳዊትም ያንን ውኃ አፈሰሰው “ለምን አፈሰስከው?” ቢሉት “ደማችሁን መጣጠት አይደለምን?” ብሎ፤ ይህም ከጽድቅ ገብቶ ተቆጠረለት፡፡ 2ሳሙ.23፥13-17

አባቶቻችን ይህንን ሲያመሰጥሩት የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ አባታችን አዳም ከተድላ ገነት ወደ ምድረ ፋይድ፥ ከነጻነት ወደ መገዛት፥ ከልጅነት ወደ ባርነት፥ በወረደና  ፍትወታት እኩያት ኀጣውእ በጠላትነት በተነሱበት ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተገኘ ከጌታ ጎን የተገኘ ማየ ገቦ አመጡለት ማለትም የአዳም ልጅነት በከበረው የክርስቶስ የደሙ ፈሳሽነት የሥጋው መሥዋዕትነት ተመለሰለት፡፡ ይህንን ለአዳምና ለልጆቹ የባህርይ አምላክ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን ፀዋትወ መከራ እያሰቡ ሰማዕታት በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጥለው “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ሰገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” ብለው ደማቸውን አፈሰሱ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፡፡ /ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ዘሐሙስ/

“ሰማዕት” ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡ ይህ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ማፍሰስ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፥ የዳዊት ወታደሮች ስለ ዳዊት ፍቅር ብለው “ደማችን ይፍሰስ” እንዲሉ፤ ዳዊትም ያመጡለትን ውኃ መጠጣት ደማችሁን እንደመጠጣት ነው ብሎ በፍቅር ምክንያት ውኃውን እንዳፈሰሰው፥ ይህም ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት፥ የእግዚአብሔር ወዳጆች የሆኑ ቅዱሳን ሰማዕታትም እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ሃይማኖት የሆነችው እውነተኛይቱን ሃይማኖት ወደው ደማቸውን አፈሰሱ፣ አጥንታቸውን ከሰከሱ፣ ስለዚህ እንደ ፀሐይ አብርተው በሰማያት ዛሬም ስለ እኛ እየማለዱ አሉ፡፡ “ለመሆኑ ከዚህ ክብር የደረሱት እንዴት ነው?” ብሎ ለሚጠይቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሲመልስ ሦስት ነገሮችን ያነሣል፡፡

1.    “ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ” ይላል
ዓለም እንደየዘመኑ የተለያየ ጠባይ አላት፤ ልክ እንደ እስስት ትለዋወጣለች፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ከእውነት ይልቅ ሐሰት፥ ከፍቅር ይልቅ በእውነተኞቹ ላይ ጥላቻ፥ በግልጽ ይታይባታል፡፡ የራሷ የሆነውን እጅግ አድርጋ ትወዳለች ስለዚህም በተለያየ መረብ እያጠመደች ለዘለዓለሙ ትጥላለች፡፡ “ሰማዕታት” /ምስክሮች/ ግን የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ማለትም እውነት እግዚአብሔርን፥በሐሰት ጣዖት አልለወጡም ስለዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ በክብር ተቀምጠው ስለ እኛ እያማለዱ አሉ፡፡ ትምህርታችንን የበለጠ ግልጽ እንዲያደርግልን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሸዋ ቁጥራቸው ከበዛ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ካላቸው ቅዱሳን ሰማዕታት መካከል የሰማዕታት አለቃ ተብሎ በፈጣሪው በእግዚብሔር ዘንድ ስለተሾመው ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጋድሎ ሕይወት ጥቂት እንመለከታለን፡፡

በረከቱ ይደርብንና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቱ ስም ዘሮንቶስ የእናቱ ስም ቴዎብስታ ይባላል፡፡ አባቱ በፍልስጥኤም አገር መስፍን ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕፃን ሳለ አባቱ በሞት ተለየው ከዚያ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሹመት ለመቀበል ወደ ዱድያኖስ ንጉሥ ዘንድ ሄደ፡፡ ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲያመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው፡፡ ይህንን አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ፤ በእርሱ ዘንድ ያለውን ለንጉሡ እጅ መንሻ ያመጣውን ገንዘቡን ለድሆች እና ለምስኪኖች ሰጠ፡፡ ባሮችንም ነጻ አወጣቸው ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ “በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ በግልጽ እኔ ክርስቲያን ነኝ” አለ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡ ዱድያኖስ በዘመኑ ከነበሩ በሥልጣኑ በሥሩ ከሚተዳደሩ 70 ነገሥታት ጋር ሆኖ አባብለው እግዚአብሔርን እንዲክድ ለጣዖት እንዲሰግድ ይህንን ቢያደርግ ብዙ ብር እና ወርቅ እንደሚሰጠው ከእርሱም በታች ባለ ሥልጣን እንደሚያደርገው ቃል ገባለት፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ይህንን አልተቀበለም፡፡ በፊቱ ናቀው እንጂ ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” ማቴ.16፥26 እንዳለ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በወጣትነቱ እግዚአብሔርን ክዶ ለጣዖት ሰግዶ የሚያገኘውን ወርቅ እና ብር እንዲሁም ሥልጣን ናቀ፡፡ ይህ እግዚአብሔር ለማገልገል በሕይወቱ ያሳየውን ቆራጥነት እራስን መካድን ያሳየናል፡፡ ማቴ.16፥24፡፡ ከዚህ ቅዱስ ሕይወት ተምረን እኛም በዓለም ውስጥ ከሚሠራው የኀጢአት ሥራ በንስሐ ሕይወት በጽድቅ ሥራ መለየት ይገባናል በዘመናችንም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዓለምን ጣዕም መናቅ ማለት እውነትን በሐሰት አለመለወጥ ማለትም እውነተኛ ሆኖ መገኘት የሚበላውን ከማይበላው ጋር ቀጥቅጦ አለመሸጥ በሚዛን አለመበደል ፍርድ አለማጉደል ጉቦ ተቀብሎ ድኃ አለመበደል በምንሠራበት መሥሪያ ቤተ ሰነድ አለመሰረዝ አለመደለዝ ባጠቃላይ በሕይወታችን በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ በእውነት ታምነን መገኘት ይገባናል፡፡ ለዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎትና ምልጃ ይርዳን፡፡

2.    ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ
እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ዱድያኖስ ንጉሥ የዚችን ዓለም ጣዕም አቅምሶ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማባበል ለጣዖት ማሰገድ በተሳነው ጊዜ የወሰደው እርምጃ በዘመኑ በነበረው የተለያየ መሣሪያ ተጠቅሞ የቅዱስ ጊዮርጊስን ደም ማፍሰስ ነበር፡፡ በገድለ ጊዮርጊስ እንደተጻፈ ለቆመው የወርቅ ምስል አልሰግድም እነርሱንም አላመልክም ይልቁንም ዐይን እያላቸው የማያዩ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ እግር እያላቸው የማይሄዱ በአፋቸው ትንፋሽ የሌለ ግዑዛን ናቸው፡፡ እነርሱን የሚያመልኩ እንደነርሱ ይሁኑ ብሎ በቅዱስ ዳዊት ቃል ንጉሡን እና ጣዖታቱን በዘለፈ ጊዜ መዝ.113፥12-16 ዱድያኖስ ንጉሥ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስገረፈው በተገረፈ ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከዚያም ጨለማው ጥልቅ ወደ ሆነ የእስር ቤት ጣሉት፡፡ ዱድያኖስና ሰባው ነገሥታት በዚህ መከራ ይሞታል የእርሱን መከራ መቀበል የደሙንም መፍሰስ የተመለከቱ ሌሎች ሰዎችም በመፍራት በእኛ የጣዖት አምልኮ ሥርዓት ፀንተው ይኖራሉ ብለው አስበው ነበር፡፡

ነገር ግን የቅዱስ ጊዮርጊስን መከራ መቀበል የደሙንም መፍሰስ የወደደ ይህንንም ለክብር ሊያደርግለት ፈቃዱ የሆነ ቅዱስ እግዚአብሔር በግርፋቱና በደሙ መፍሰስ እንዲሞት አልተወውም ስለዚህ ወደ እስር ቤቱ የጨለማውን ጥልቀት በብርሃን የሚገልጥ ቁስሉንም የሚፈውስ የሚያጽናና መልአክ ላከለት፤ መልአኩም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብቶ ቁስሎቹን ፈወሰ፤ እርሱንም አጽናንቶ ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ ያደረገለት ያለውን ሁሉ በግልፅ ነግሮት በክብር አረገ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ሲነጋ የዱዲያኖስ ወታደሮች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጡ ጊዜ ምንም የግርፋትና የደም መፍሰስ ምልክት ባላገኙ ጊዜ፣ ይልቁንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግን  አግኝተው ተደነቁ፡፡ ከዚያም “እኛም በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እናምናለን፡፡” ብለው ብዙ ሰዎች ሰማዕትነት ተቀበሉ፡፡አንድ ዛፍ በተቆረጠ ጊዜ ከስሩ ብዙ ችግኝ እንዲገኝ በቅዱስ ጊዮርጊስ መከራ መቀበል ብዙ ሰዎች ወደ ሃይማኖት መጡ፡፡

3. ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ
ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲህ ያለውን ተአምት በማድረግ ብዙ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ የተመለከተ ዱድያኖስ አሁንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የሚደርሰውን የመከራ ስልት በመቀያየር አትናስዮስ የተባለ ጠንቋይ አስመጥቶ መርዝ በጥብጦ እንዲጠጣ አዘዘ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የቀረበለትን መርዝ በሰው ሁሉ ፊት በትእምርተ መስቀል አማትቦ ባጣጣመ ጊዜ እንኳን ሊገድለው ገፁ ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርቶ ተገኘ፡፡ በዚህም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ላይ “በስሜ የሚያምኑትን ይህች ምልክት ትከተላቸዋለች…የሚገድል መርዝ ቢጠጡ አይጎዳቸውም ” በማለት የተናገረው ቃል ተፈጸመለት፤(ማር.16፥18)፡፡ ይህንን ተመልክተው ጠንቋዩን ጨምሮ ብዙ ሰዎች “በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እናምናለን” ብለው ከአምልኮ ጣዖት እግዚአብሔርን ወደማምለክ ተመልሰው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡

በዚህ ነገር የተበሳጨ ዱድያኖስ በብረት ምጣድ እሳት አንድደው እንዲያቃጥሉትና ካሳረሩት በኋላ  በመንኮራኩር እንዲፈጩት ከዚያም ይድረስ ወደ ሚባል ታላቅ ተራራ ወስደው በንፋስ እንዲበትኑት አዘዘ እንደ ትእዛዙም አደረጉበት አጥንቶቹን ፈጭተው በበተኑት ጊዜ ከተራራው ሥር የነበሩ ዕፀዋት በቅጠላቸው ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔ እያሉ ተናገሩ /መሰከሩለት/ በዚህ ጊዜ መራራ የሆነውን የሞት ጽዋ ተጎንጭቶ ከባድ መከራ ተቀብሎ እንዲሞት የእግዚብሔር ፈቃዱ ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስን ክብር እርሱን ፍፁም መውደዱን ለመግለጽ አምላካችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅዱስት ድንግል ማርምን ባለሟሎቹ ቅዱሳን መላእክትን ወዳጆቹ ነቢያት ሐዋርያት ቅዱሳንን አስከትሎ አፅሙ ወደ ተዘራበት ወደ ይድራስ ተራራ ወረደ በክብር ወረደ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልን አዘዘው የተበተነው የወዳጄን የቅዱስ ጊዮርጊስን አፅም ስብሰባህ አምጣ አለው እርሱም እንደታዘዘው ሰበስቦ ወደ ጌታችን አቀረበ ያን ጊዜ ጌታችን በምሕረት እጁ ተቀብሎ  አዳምን የፈጠሩ እጆቼ አንተንም የፈጠሩ አሁንም ወዳጄ ጊዮርጊስ እኔ አዝዤአለሁ ከሞት ተነሣ አለው፡፡ ያን ጊዜ ከጫጉላ ቤት እንደሚወጣ ሙሸራ አምሮበት ከሞት ተነሣ ጌታችንም በአፍ መሳም ሳመው የሚጸናበትን ቅዱስ መንፈሱን አሳደረበት ከዚያም ሊቀበለው ያለውን መከራ የሚያገኘውን ዋጋ ነግሮት በክብር አረገ፡፡

ይህ የሆነው ጥር 18 ቀን ነው፡፡ ይህንን መራራ ሞት በእሳት መቃጠል በመንኮራኩር መፈጨት እንደ እህል መዘራት ታግሶ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተደረገለት ተአምራት ከሞትም በመነሣቱ ብዚ ሰዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አምነው ወደ እውነተኛይቱ ሃይማኖት ተመልሰዋል፡፡ እንግዲህ በገድሉ መጽሐፍ እንተጻፈ ለ7 ዓመት መራራ መራራ የሆነ ብዙ መከራዎችን ታግሶ በስተመጨረሻ በሰይፍ ተከልሎ /አንገቱን ተቆርጦ ከአንገቱም ደም ውኃ ወተት ፈሶ ለተጋድሎው 7 የድል አክሊል ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለ የከበረ ቃል ኪዳን የተቀበለ ሰማዕት ነው፡፡ እኛም ከዚህ ቅዱስ ገድል ተምረን አሰረ ፍኖቱን በመከተል ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እንድናጸና ዘመኑ የሚጠይቀውን ሰማዕትነት ምግባር ማቅናት እንድናቀና የሠማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎትና ቃል ኪዳን ተራዳኢነት አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችን አማላጅነት የቅድስት ሥላሴ ቸርነት አይለየን አሜን፡፡
ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ለማ በሱፈቃድ

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ  የመሳሰሉትን ፍች ይይዛል፡፡ ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥር ወር በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባልም ይታወቃል ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት/የታየበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ዘመነ አስተርእዮ ተባለ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠው  በዚሁ ወር ነውና ዘመነ አስተርአዮ ተብሎ ይጠራል፡፡


በዚህ ጽሑፍ የምናተኩረው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ የመታየቱ/የመገለጡ ዋና ዋና መክንያቶቹ ምንድናቸው የሚለው ነው፡፡

1.    የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ
እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ በክብር ይኖር ዘንድ ገነትን አወረሰው፡፡ በማየት የሚደሰትበትና የሚማርበትንም ሥነ ፍጥረትን ፈጠረለት የሚበላውንና የማይበላውንም ለይቶ ሰጥቶት ነበር ነገር ግን የሰው ልጅ አትብላ ያለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሳይጠብቅ የተከለከለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ምክንያት ከገነት ተባረረ፡፡ ዘፍ.2፥16 በዚያን ጊዜ ነው ርህራሄ የባህርዩ የሆነ አምላክ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው የሚለው የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጠው ሲራ.24፥6፡፡

አዳምም ከነ ልጆቹ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት ይህንን ቃል ኪዳን ሲጠባበቅ ኖሯል፡፡ ነቢያቱም ትንቢት ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች በማለት ተስፋውን በትንቢተ ነቢያት በማስታወስ ቆይቷል፡፡ ኢሳ.7፥14

በዚህ ዘመን ደቂቀ አዳም በሙሉ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዘው ተስፋውን ሲጠባበቁ የነበሩበት ዘመን ከዚሁ የጭለማ ዘመን ለመዳን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ውጤት ያላመጣ ነበርና ጊዜው/ ቃል ኪዳኑ እስኪፈጸም ድረስ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፡፡ ኢሳ.26፥20 ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ ተብሎ እንደተጻፈው ይህችን ቃል ኪዳን ይፈጽማት ዘንድ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ በሥጋ ተገለጠ ማለት ሥጋን ተዋሐደ፡፡

2.    የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ
ወዘሰ ይገብራ ለኀጢአት እምነ ጋኔን ውእቱ እስመ ቀዳሚሁ ለሰይጣን አበሰ ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሰዐር ግብሮ ለጋኔን” ኀጢአትን የሚሠራትም ከዲያብሎስ ወገን ነው፡፡ ጥንቱንም ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ 1ዮሐ.3፥8 በማለት ሐዋርያው እንደገለጸው ሰይጣን የሰውን ልጅ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን የመሰለ ቦታ እንዲያጣ ከደስታ ወደ ዘለዓለም ሐዘን ከነጻነት ወደ ግዞት ከብርሃን ወደ ጨለማ ይገባ ዘንድ ረቂቅ ሥራ ሠርቶ ነበርና ይህንን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ/በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ነገት ገብቶ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ የደያብሎስን ሥራ አፍርሶበታል፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን አስቶ የግብር ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለደያብሎስ ብለው የፈረሙትን ደብዳቤ በዮርዳኖስና በሲዖል የቀበረውን የጥፋት የተንኮል ሥራውን ያፈርስ ዘንድ ሰው ሆኖ ተገለጠ፡፡ ይህንን የዲያብሎስ ሥራ በዮርዳኖስ ባሕር የተቀበረውን በጥምቀቱ በሲዖል የተቀበረውን በስቅላቱ በሞቱ ደምስሶበታልና “ወነስተ አረፍተ ማእከል እንተ ድልአ በሥጋሁ” በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፈረሰ፡፡ ኤፌ.2፥14 በማለት ሐዋርያው እንደተናገረው የዲያብሎስን ክፉ ሥራ የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡

3.    አንድነት ሦስትነቱን ይገልጥ ዘንድ
የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጥ አይታወቅም ነበር የተገለጠ የታወቀ የተረዳ የአንድነቱን ሦስትነቱን ትምህርት በሚገባ ለማስተማር የተቻለው ጌታችን ሥጋ ለብሶ ከተጠመቀ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ “ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ በአምሳለ ርግብ ወናሁ መጻአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ ለመሥዋዕትነት የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፡፡ ማቴ.3፥17 /ሉቃ.3፥21፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል አብ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚለው ቃል በተገለጸ ጊዜ  የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ይሽር ዘንድ የአንድነት እና ሦስትነት ምሥጢር ገልጿአል፡፡ ይህንን ምሥጢር ይገልጠ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ ታየ፡፡ ይህ ምስጢር ጥንተ ዓለም ሳይታወቅ ሳይገለጥ ተሰውሮ ይኖር ነበር፡፡ በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅቡእ ኅርመቱ እምቅድመ ዓለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ተሰውሮ ነበር ከነቢያት ቃል የተነሣ በዚህ ዘመን ተገለጠ፡፡ ሮሜ.16፥24

4.    ፈጽሞ እንደወደደን ለመግለጽ
እግዚብሔር ሰውን ምን ያህል እንደወደደ ለመረዳት እግዚብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነውና ማንም ሳያስገድደው ሰው ሁን ብሎ ሳይጠይቀው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑን ጠብቆ ሰው ሆኖ ከኀጢአት በስተቀር ሁሉን ፈጽሞ በገዛ ፈቃዱ መከራ ሥጋን ተቀብሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ የዘለዓለም ሕይወትን መስጠት ምን ያህል ፍጹም ፍቅሩን እንደገለጸልን እንረዳለን፡፡ “አልቦ ዘየዐቢ እምዝ ፍቅር ከመ ዘቦ ዘይሜጡ ነፍሶ ህየንተ አእርክቲሁ” ስለወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም ዮሐ.15፥12 ያጠፋው የሰው ልጅ ይሰቀል ይሙት ሳይል እኔ ልሙት ማለት ፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ሰው ሰውን የሚወደው ገንዘቡንና የመሳሰሉትን እስከ መስጠት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚወድ የለም አልነበረም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ መኪራ ሥጋን ተቀብሎ ሰውን በሞቱ ያድን ዘንድ ሞትን የሞተው ፈጽሞ እንደወደደን ለመግለጥ ነው፡፡ 1ዮሐ.4፥9፡፡ ይህም ፍቅሩ ይቃወቅ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስለዚህ ሊቃውንቱ አስተርእዮ በማለት ሰይመውታል፡፡